Exodus 15

የሙሴና የማርያም መዝሙር

1ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘመሩ፤

“ከፍ ከፍ ብሎ ከብሯልና፣
ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እዘምራለሁ፤
ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣
በባሕር ውስጥ ጥሏልና።

2እግዚአብሔር (ያህ) ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤
ድነቴም ሆነልኝ፤
እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ፤
የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
3 እግዚአብሔር (ያህዌ) ተዋጊ ነው፤
ስሙም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው።
4የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣
ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤
ምርጥ የሆኑት የፈርዖን ሹማምት፣
ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጠሙ።
5ቀላያትንም ለበሱ፤
እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረዱ።
6አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤
ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤
አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤
ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ።

7“በግርማህ ታላቅነት፣
የተቃወሙህን ጣልኻቸው፤
ቍጣህን ሰደድህ፤
እንደ ገለባም በላቸው።
8በአፍንጫህ እስትንፋስ፣
ውሆች ተቈለሉ፤
ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤
የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ።
9ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤
እማርካቸዋለሁ፤
ምርኮን እካፈላለሁ፤
ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤
ሰይፌን እመዝዛለሁ፤
እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።’
10አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤
ባሕርም ከደናቸው፤
በኀያላን ውሆች፣
እንደ ብረት ሰጠሙ።
11አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤
ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ?
በቅድስናው የከበረ፣
በክብሩ የሚያስፈራ፣
ድንቆችን የሚያደርግ፣
እንደ አንተ ማን አለ?

12“ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤
ምድርም ዋጠቻቸው።
13በማይለወጠው ፍቅርህ፣
የተቤዥሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤
እነርሱን በብርታትህ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ።
14አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤
የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል።
15የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤
የሞአብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤
የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ።
16አቤቱ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ሕዝብህ
እስከሚያልፉ ድረስ፣
የተቤዠኻቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣
ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤
በክንድህ ብርታት፣
እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ።
17 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ማደሪያህ
እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣
ጌታ (አዶናይ) ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣
በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም።

18እግዚአብሔር (ያህዌ)
ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
19የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና
ወይም፣ ሠረገለኞች
ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ።
20ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። 21ማርያምም፣

“ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣
በባሕር ውስጥ ጥሏል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤
እጅግ ከፍ ከፍ ብሏልና”
እያለች ዘመረችላቸው።

የማራና የኤሊም ውሃ

22ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። 23ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው።
ማራ ማለት መራራ ማለት ነው።
24ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ።

25ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ።

በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው።
26እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝና።”

27ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።

Copyright information for AmhNASV